The management and employees of EIC planted trees

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥራ አመራርና ሠራተኞች ችግኝ ተከሉ

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በዘንድሮው ክረምት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ6ኛ ጊዜ በሚደረገው «የአረንጓዴ አሻራ» መርሃ ግብር ላይ ሀገራዊ ጥሪውን በማክበር ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የድርጅቱ ጽ/ቤቶች፣ዲስትሪክቶችና ቅርንጫፎች የተውጣጡ ሠራተኞች በተገኙበት በአያት ኮንዶሚኒየም መድኃኔዓለም ጸበል  አጠገብ  ባዘጋጀው የተራቆተ ቦታ ላይ ለ2ኛ ጊዜ አምስት ሺህ የሚሆኑ ችግኞችን ተከለ፡፡

አቶ ነፃነት ለሜሳ የችግኝ ተከላ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ሲያደረጉ

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ በችግኝ ተከላው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ገለጻ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በየዓመቱ አጠናክረን በማስቀጠል የሀገራችንን የደን ሽፋን ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ ያስችል ዘንድ ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተረከቡትን የተራቆተ ቦታ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት በማልማት ለክፍለ ከተማው እንደሚያስረክቡ ቃል መግባታቸውን በመግለጽና በ2013 ዓ.ም የተተከሉ ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ በማግኘታቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መጽደቃቸውን በመጥቀስ በዘንድሮው ክረምት ለተተከሉ ችግኞች ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመውሰድ ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ በማድረግ በቀጣይ ሌሎች የተራቆቱ ቦታዎችን በማልማት የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል በሚያስችል ደረጃ የተጎዱ ቦታዎችን በማልማት ድርጅቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

አቶ ነፃነት ለሜሳ አክለውም በሀገራችን በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ ምንም እንኳን በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ያላደረሰ ቢሆንም በብዙ አርብቶ አደሮች በተለያዩ አካባቢዎች በእንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱ የደኖች መመናመን መሆኑን እንደዋነኛ መንስኤ  በማንሳት የሀገራችንን የደን ሽፋን ወደነበረበት ለመመለስ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ ብዙም ያልዘገየና በቀጣይ እያንዳንዱ ግለሰብ አካባቢውን በማልማት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡  

የኢ.መ.ድ ሰራተኞች የችግኝ ተከላ ክንውን በከፊል