የኢትዮጵያ መድን ድርጅት
የሰብል ምርት መቀነስ የመድን ሽፋን በአዲስ መልክ መስጠት ጀመረ
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ነሀሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ አርሲ ዞን አዳባ እና ባዶባሳሳ አካባቢ ለሚገኙ ስድስት መቶ አርሶ አደሮች የድርጅቱ የበላይ አመራሮች፣ የወረዳው መስተዳድሮች፣ የጃይካ አመራሮች እንዲሁም የወረዳው አርሶ አደሮች በተገኙበት ከምርት መቀነስ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የሰብል ምርት እጥረት የሚሰጠውን ሽፋን በአዲስ መልክ የማስተዋወቅና ሽፋኑን ለገዙ አርሶ አደሮች ሰርተፊኬት የመስጠት ሥነ-ሥርዓት አከናውኗል፡፡
በሙከራ ትግበራው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋ/ሥ/አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ እንዳሉት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለ47 ዓመታት የመድን ሽፋን እየሰጠ ያለ ሲሆን ቀድሞ ከሚሰጠው የህይወት፣ የንብረትና የህጋዊ ሃላፊነት ዋስትና በተጨማሪ ወቅቱ የሚፈልገውን ሽፋን በጥናት በመታገዝ ለመላው ሀገሪቱ ገበሬ ስጋት የሆነው በዝናብ፣ በበረዶ፣ በእሳትና በተለያዩ ምክንያቶች ለሚከሰት የሰብል ምርት ውድመት ለሚፈጠር ማህበራዊ ቀውስ ሽፋን የሚሰጥና የገበሬውን ስጋት ከመቅረፉም በተጨማሪ ለሀገር ኢኮኖሚም ድጋፍ የሚውል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ድርጅቱ የሰብል መድን ኢንሹራንስ በማይክሮ ኢንሹራንስ ቢሮ በኩል መስጠት ከጀመረ የቆየ መሆኑን ገልጸው ይህ የሙከራ ትግበራ በዋናነት የመንግስትን ስትራቴጂ ለማስፈጸም ተዘጋጅቶ የተቀረጸ ሰፊ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረው ገበሬው ከሚጓጓለት ሰብል ማግኘት የሚገባውን ምርትም ሆነ ጥቅም ሳያገኝ ሲቀር ወጪውም ሆነ የህልውና ጫናው በላዩ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ እንዳይጎዳው ማህበረሰቡን ለማገዝ የግብርና ፖሲሲን ጭምር ለማስፈጸም የተዘጋጀ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
የሙከራ ትግበራው ከተለያዩ ባንኮች ጋር በመተባበር የሚከናወን መሆኑን ሲገልጹ የውል ክፍውያውም ሆነ የካሳ ክፍያው በሞባይል ባንኪንግ እና በቴሌ ብር እንደሚከናወን ገልጸው ይህ የሙከራ ትግበራ እውን ይሆን ዘንድ ከኢ.መ.ድ ጋር አብረው የሰሩ አካላትን በዋነኝነት ጃይካ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ የወረዳው መስተዳድሮች፣ ቀበሌዎች፣ የማህበራት ሰራተኞች እንዲሁም ጥሪውን ተቀብለው ለሙከራ ትግበራው ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ለወረዳው አርሶ አደሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ለዚህ ሽፋን ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ እንዲሳተፍ በማሳሰብ ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡